Amharic Tube - All Amharic TV Channels and Shows
Welcome
Login

Russia foreign minister to visit Ethiopia የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በመጪው መስከረም ወር ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ፡፡ 

ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚስተር ላቭሮቭ ለሁለት ቀናት ይፋ ጉብኝት በመስከረም ወር አጋማሽ ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሆነ የገለጹት ምንጮች፣ ከፍተኛ የሩሲያ የንግድ ልዑክ ከሚስተር ላብሮቭ ጋር እንደሚመጣ አስረድተዋል፡፡ 

ሚስተር ላቭሮቭ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ግንኙነቶች የሚመክሩ ሲሆን፣  የትብብር ስምምነት ይፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

ሚስተር ላቭሮቭ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን በ1998 ዓ.ም. ጎብኝተው እንደነበረ  ሲታወስ፣ ይህ ሁለተኛ ይፋ ጉብኝታቸው ይሆናል፡፡ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት የሩሲያ አምራች ኩባንያዎች፣ የኢነርጂና የነዳጅ ኩባንያ ተወካዮች በንግድ ልዑኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የሩሲያ ኩባንያዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢነርጂና በነዳጅ ፍለጋ ሥራዎች ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል ተብሏል፡፡ 

በቅርቡ ‹‹ጂቢፒ›› ግሎባል ሪሶርስ የተሰኘ የሩሲያ የነዳጅ ኩባንያ በአፋር ክልል የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ለማካሄድ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ሶሻሊዝም በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ በነገሠበት ወቅት የቀድሞ ሶቭዬት ኅብረት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የነዳጅና የማዕድናት ፍለጋ ዘርፍ በርካታ ሥራዎች ሠርተዋል፡፡ 

በ1970ዎቹ ሶቭዬት ፔትሮሊየም ኤክስፕሎሬሽን ኤክስፒዲሽን የተሰኘ ኩባንያ ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ፍለጋ ድርጅት ጋር በመተባበር ኦጋዴን ውስጥ ሰፊ የሆነ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ሠርቷል፡፡ 

በተጨማሪም በማዕድን ዘርፍ ሩሲያውያን ውጤታማ ሥራ አከናውነዋል፡፡ በቦረና ዞን ቀንጢቻ አካባቢ የሚገኘውን የታንታለም ክምችት ያገኙት የሶቭዬት ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ ሚድሮክ ጐልድ ወርቅ የሚያመርትበት በለገደንቢ የሚኘውን የወርቅ ክምችት ያገኙት የሶቨዬት ኅብረት ባለሙያዎች ከኢትዮጵያውያን ጂኦሎጂስቶች ጋር በመተባበር ነበር፡፡ 

በባሌ የሚገኘው የመልካ ዋከና የኃይል ማመንጫ ጣቢያና በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የኤልዌሮ የመስኖ ግድብ የተገነቡት በሶቭዬት ኅብረት መሐንዲሶች ነበር፡፡ የናዝሬት ትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ የተገነባው እንዲሁ በሶቭዬት ኅብረት ባለሙያዎች ነበር፡፡ 

ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት አሁን ሩሲያውያን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በማኑፋክቸሪንግ፣ በኃይል ማመንጨት፣ በማዕድን ፍለጋና ልማት እንዲሁም በነዳጅ ፍለጋ የመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ላቭሮቭ የሚመራው ልዑክ ዋና ዓላማም ለዚህ ዕቅድ መሠረት መጣል ነው፡፡ የሩሲያ ልዑካን ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ጋር ተገናኝተው በኢነርጂ መስክ ስላለው የኢንቨስትመንት ዕድል እንደሚመክሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት 30 የሚደርሱ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተሳታፊ ናቸው፡፡ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ሥራ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከሩሲያ መንግሥት ለባቡር ፕሮጀክቶች የሚውል ብድር ለማግኘት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ 

ኢትዮጵያ የተለያዩ የግብርና ውጤቶች ወደ ሩሲያ ትልካለች፡፡ የኢትዮጵያ አበባ አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ወደ ሩሲያ ለመላክ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሩሲያ ትልቅ የአበባ ገበያ ያለ ቢሆንም፣ ሩሲያውያን የኢትዮጵያን አበባዎች የሚገዙት በቀጥታ ከኢትዮጵያ ላኪዎች ሳይሆን ከሆላንድ የአበባ ገበያ ነው፡፡ 

ይህን ጉዳይ ያጠናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ሞስኮ የመንገደኞችና የካርጎ በረራ ለመጀመር ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ሩሲያ ከንግድና ኢንቨስትመንት በተጨማሪ በውትድርና መስክ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአብዛኛው የታጠቀው ሩሲያ ሠራሽ መሣሪያዎችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሚጠቀምባቸው ተዋጊ ጄቶች፣ ሔሊኮፕተሮችና የጭነት አውሮፕላኖች በሙሉ በሩሲያ የተፈበረኩ ናቸው፡፡ 

የሚስተር ላቭሮቭ ጉብኝት አስመልክቶ አዲስ አበባ ከሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሚስተር ላቭሮቭ በመስከረም ወር አዲስ አበባን እንደሚጎበኙ አረጋግጠዋል፡፡ 

የኢትዮጵያና የሩሲያ ታሪካዊ ግንኙነት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የዘለቀ ነው፡፡ ታዋቂው የሩሲያ ጸሐፊ አሌክሳንደር ፑሽኪን ወንድ አያቱ ኢትዮጵያዊ መሆን የሁለቱ አገሮች የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ኃይሎች በተወረረች ቁጥር ሩሲያውያን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ይታወቃሉ፡፡ ለዚህም በዓድዋ ጦርነት ወቅት የሩሲያ ቀይ መስቀል ለኢትዮጵያ አርበኞች ያደረገው የሕክምናና የመድኃኒት ዕርዳታ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ 

ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜላችሁን አስመዘግቡ።

 

Post your comment

Comments

Be the first to comment
Watch new Ethiopian movies. Visit the new Sodere.com website or download the mobile application for iPhone and Android. Choose your phone type. iPhone   Android     iPad

Related Articles

RSS