Amharic Tube - All Amharic TV Channels and Shows
Welcome
Login

የፍልፍሉና የቁልሉ ጨዋታ በጣም አስቂኝ ቃለ ምልልስ Very Funny Interview with Filfilu

(ዘ-ሐበሻ) ቁልሉ (ወንደሰን አውራሪስ) ከፍልፍሉ (በረከት በቀለ) ጋር ብዙ ጊዜ አብሮ የሰራ ኮመዲያን ነው፡፡ ዛሬ ግን ቁልሉ ጋዜጠኛ በመሆን ፍልፍሉን ይጠይቀዋል፡፡ እነሆ ቃለ – ምልልሳቸው፡-
ቁልሉ፡- ልጀምር?
ፍልፍሉ፡- ፊሽካ እስኪነፋ ነው የምጠብቀው?
ቁልሉ፡- ታዲያ ምነው ፊትህ ሾለ?
ፍልፍሉ፡- ያንተን ፊት ስፋት አይቼ እንዳንለያይ ብዬ ነው፡፡
ቁልሉ፡-የእኔ ፊት እኮ መሬት በሽጉጥ መሳት ነው፡፡
ፍልፍሉ፡- የታወቀ ነው፡፡ ይልቅ ወደ ቁም ነገሩ እንግባ… እንግዲህ ብዙ ጊዜ ጋዜጠኞች አርቲስቶችን ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ገጠመኝ የሚጠይቁት መጨረሻ ላይ ነው፡፡ እኛ እስቲ ለየት እናድርገውና እዚህ ጋር ገጠመኛችንን እናውራ?
ቁልሉ፡- በጣም ጥሩ ነው…የሆነ ጎደኛዬ ነበር፡፡ አሁን ውጪ ሃገር ሄዷል፡፡ ብዙ ጊዜ አብረን ነበር የምንሠራው፡፡ ሰዎች በመንገድ ሲያገኙን ግን ለእኔ ነው አድናቆታቸውን የሚገልፁልኝ ‹‹ማታ ቲቪ ላይ አየንህ ጥሩ ነው›› ይሉኛል፡፡ በዚህ ጊዜ አብሮኝ ስለሠራ እሱንም እንዲያደንቁት ‹‹እሱም አብሮኝ ነው የሠራው›› አልኳቸው፤ በዚህ ጊዜ ‹‹እሱን አናውቀውም አንተን ነው›› ሲሉኝ በጣም ተናደደ፡፡ ላረጋጋው ስሞክር ይባስ ተበሳጭቶ ‹‹እንዴት እኛ እንታይ… ይህን የሚያክል 21 ኢንች ፊት ይዘህ እንዴት እንታይ›› አለኝ፡፡
ፍልፍሉ፡- ታዲያ ስክሪኑን ስትሞላበት ምን ያድርግ.. ይኸው እኔን ራሴን መንገድ ላይ እየከለልከኝ ተቸግሬ የለ…
ቁልሉ፡- እኔ ፊት ለፊት ነው የከለለልኩት አንተስ በጎን እየሸፈንከኝ አይደል… እንደ ዶሮ፡፡… አንተ ግን ፍልፍሉ ለምን ተባልክ?
ፍልፍሉ፡- ፍልፍሉ የተባልኩት ከብዙ ዓመታት በፊት በክበባት ውስጥ እሳተፍ በነበረ ጊዜ የሆነ ነገር እፈለፍላለሁ፡፡
ቁልሉ፡- ነገር መፈልፈልማ አሁንም አብሮህ ነው፡፡
ፍልፍሉ፡፡- አዎ! ሆቢዬ ነው!… እና በዚያ ሠዓት አስተያየትና ትችት ሣቀርብ ብዙዎች ያላዩትንና ያላስተዋሉትን ነገር ነው የማነሳው፡፡ በዚህ ወቅት ነው አንድ የክበባችን አባል ‹‹ይሄ ልጅ ነገር ይፈለፍላል›› ያለችኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ፍልፍሉ የተባልኩ ይኸው እስከዛሬ እየፈለፈልኩ ተቀምጫለሁ፡፡ አንተስ ቁልሉ የተባከው እንዴት ነው?
ቁልሉ፡- መልስህ እኔኑ ትጠይቀኛለህ?… ብዙ ድራማዎችን የሠራሁት ወንደሰን አውራሪስ በሚለው ዋና ስሜ ነው፡፡ ቁልሉ ብለህ ያወጣህልኝ አንተ ነህ… ስለዚህ ለምን ቁልሉ እንዳልከኝ ራስህ ተናገረው፡፡
ፍልፍሉ፡- እኔ ነገር ስፈለፍል አንተ ተቆልለህ ነው የምታየው፡፡ ለዚህ ነው፡፡
ቁልሉ፡- ብዙ ሰዎች የድሮ ትዝታቸውን ሲናገሩ እንትና የሚባል ጎደኛ ነበረኝ አሁን ውጪ ሃገር ሄዷል፡፡ እንትና የሚባል ልጅ ነበር አሁን አውሮፓ ነው ያለው እያሉ ያወጋሉ፡፡ አንተ ግን ብዙ ጊዜ ስትናገር ‹‹እንትና የሚባለው ጎደኛዬ ነፍሱን ይማረውና፣›› ‹‹እከሌ የሚባል ልጅ ነፍሱን በገነት ያኑረውና›› እያልክ ስትናገር ነው የምሰማህ፡፡ አንድም ‹‹በህይወት ያለ ጎደኛዬ…›› ብለህ ስትናገር አልሠማሁም፡፡ ለምንድን ነው?
ፍልፍሉ ፡- እኔንጃ!… ብዙዎቹ የእውነት ሞተው እንዳይመስልህ፡፡ በቁም የሞቱትንም እንደዚያ ነው የምላቸው፡፡ የዕውነት የሞቱትም ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ቢሆንም በህይወት ያሉ ከእኔ በበለጠ ደረጃ ላይ የሚገኙ በጣም የምወዳቸው ብዙ ጎደኞች አሉኝ፡፡… ይልቅ አንድ ገጠመኜን ልንገርህ?
ቁልሉ፡- የሚያስቅ ነው ወይስ የሚያሳዝን?
ፍልፍሉ፡- ሊያሳዝን ነው የሚችለው… አቶ ተሾመ የሚባሉ ጉረቤት ነበሩ፡፡ ቴዲ ከሚባል ልጃቸው ጋር የታሰረውን ውሻ ምንም ሳያደርገን በድንጋይ እንቀጠቅጠዋለን፡፡ ሁሌ እንዲያ ስናደርገው ቆይተን አንድ ቀን ሠንሠለቱን በጥሶ መጣ፡፡ ድንገት ስለሆነ እንዴት እንደሮጥኩ አላውቅም፡፡ ሰው ፌንጣ ሲሆን አይተህ ታወቃለህ?… ብድግ ብዬ የሆነ መስኮት ላይ ወጣሁ፡፡ ውሻው እኔን እንደማያገኝ ሲያውቅ ወደ ጎደኛዬ ዞረ፡፡ ጎደኛዬ ደግሞ በድንጋጤ ሲሮጥ ሲል ልብስ ሊታጠብበት የፈላ ውሃ ላይ በቂጡ ተቀመጠበት፡፡ እልህ ተሞልቶ ወደ ልጁ የሮጠው ውሻ የሆነውን ነገር ሲያይ ሽምቅቅ ብሎ ፊቱን አዞረና እንባውን እየዘራ ተመለሰ፡፡ ለልጁ አለቀሰለት፡፡
ቁልሉ፡- አዝኖለት ነው?
ፍልፍሉ፡- አዎ!… እኔ ውሻ ለሠው አዝኖ ሲያለቅስ ያየሁት ያን ዕለት መው፡፡ በኋላ ወደ ልጁ እየሮጥኩ ሄጄ ሳነሳው ስል ‹‹ተው አትንካኝ አበብዬን ጥራልኝ›› አለኝ፡፡ አበብዬ እናቱ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ እሳቸው እንዳይሰሙ ብዬ እንደምንም አባብዬ ሳነሳው ‹‹ሽንት ቤት ውሰደኝ›› አለኝ፡፡ ‹‹ኧረ ይሠፋብሃል›› ብዬ የነፈረውን ቂጡን በቀዝቃዛ ውሃ አበረድኩለት፡፡… ለፕሮሞሽኑም እንዲሆን እስቲ ስላወጣነው ‹‹ፍልቅልቅ›› ኮሜዲ ሲዲ እናውራ… እንዴት ነው ሠዎች ስቀውልናል? ወይስ አልቅሰውልናል?
ቁልሉ፡- እኔ የራሳችን ስለሆነ አጋነንከው አትበለኝና ስራችን በጣም ጥሩ እንደሆነ ነው የማነው፡፡ ግን እኛ ስለራሳችን ስራ ማውራት ስለሌለብን ህዝቡ እንዲፈርድ ነው መተው ያለብን፡፡ ደግሞ ህዝቡም ጥሩ አስተያየት ስለሠጠን በበኩሌ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
ፍልፍሉ፡- አዎ! አንዳንድ ሊስተካከሉና ሊታረሙ ይገባቸዋል ተብለው የተነገሩን ገንቢ አስተያየቶች እንዳሉ ሆነው በአጠቃላይ የተሠጠን ድጋፍና ሞራል ለቀጣይ ስራችን ትልቅ የሞራል ስንቅ ነበር፡፡
ቁልሉ፡- ወደ ኪነጥበብ ህይወት ስትገባ መነሻ የሆነህ ምንድን ነው?
ፍልፍሉ፡- መነሻዬ ከቤት ነው፡፡ ከቤት ተነስቼ ወጥቼ…
ቁልሉ፡- ልጠይቅህ የፈለግኩት ለኪነጥበብ ህይወትህ አርአያ (ሮል ሞዴል) ስላደረግከው ሰው ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ወደ ኮሜዲ ህይወት የተሳብኩት በደረጀና ሃብቴ ነው፡፡ አንተስ?
ፍልፍሉ፡- የእኔ መነሻዬ እማዬ ነች… አያቴ በጣም ቀልደኛ ስለሆነች የእኔ መነሻ እሷ ነች፡፡
ቁልሉ፡- አንተ በጣም ጥሩ ጭነቅላት ነው ያለህ፡፡
ፍልፍሉ፡- ኧረ!… የእኔ ከአንተ በልጦ??
ቁልሉ፡- ጭንቅላትህ ስልህ ፀጉር የሚበቅልበትን ማለቴ አይደለም፡፡
ፍልፍሉ፡- ታዲያ ጥሩ አእምሮ አለህ ነዋ የሚባው፡፡
ቁልሉ፡- እሺ!… ጥሩ አዕምሮ አለህ፡፡ ይህን የምልህ የእውነቴን ነው፡፡ ኮሜዲ በጣም ነው የምትችለው፡፡ እንደውም እኔ በድራማ መልክ ከምታቀርበው የኮሜዲ ጨዋታ ይልቅ እንዲሁ ስንጫወትና በግል ስናወራ ነው በጣም የምታስቀኝ፡፡
ፍልፍሉ፡- እኔ ግን አንተ ስትስቅ በጣም ነው የምናደደው፡፡
ቁልሉ፡- ለምን?
ፍልፍሉ፡- ባለፈው የሆነ ችግር ገጥሞኝ ደውዬ ስነግርህ የሳቅክብኝ ጊዜ እንዴት እንደተናደድኩ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡
ቁልሉ፡- ድራማ ላይ የማውቀውን ድምፅና አለቃቀስ ሠምቼ እንዴት መሳቅ ይነሰኝ?
ፍልፍሉ፡- እኔን በጣም ግራ ያጋባኝ ምሬንና ቀልዴን እንዴት እንደምለየው ነው፡፡
ቁልሉ፡- አንተ በጣም የምታሰቀኝ ከድራማ ውጪ በግል ስንጫወት ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ድራማ ከምትሠራው ይልቅ እንዲሁ ነፃ ሆነህ ስትጫወት ነው በጣም የምታሰቃቸው፡፡ በስራ ሙድ ውስጥ ስትሆን ግን አስቂኝ ነገርህ በግል ስንጫወት የምታሰቀንን ያክል አይደለም፡፡ ለምንድን ነው?
ፍልፍሉ፡- ይሄ ካሜራ የሚባለው ነገር ነፃነትህን ያናጋዋል፡፡ እኔ ካሜራ ፊት ከመቆም እልም ያለ ጦርነት ውስጥ ቆመህ ጠብቀኝ ይዤ ብገባ ነው የምመርጠው … ካሜራ በጣም ነው የምፈራው፡፡
ቁልሉ፡- ልደትህን አክብረህ ታውቃለህ?
ፍልፍሉ፡- እቅጥረዋለሁ እንጂ አክብሬው አላውቅም፡፡
ቁልሉ፡- ልደትህን በድግስ አክብረህ አታወቅም?
ፍልፍሉ፡- ሻማ ተደርድሮ እፍ… እያሉ ማጥፋት ምናምን…? አድርጌው አላውቅም፡፡
ቁልሉ፡- ለምንድን ነው?… በእናንተ ጊዜ ሻማ አልነበረም?
ፍልፍሉ፡- በል አቁም!… ዘለህ ዕድሜ ውስጥ ልትገባ ነው፡፡… ቁልሉ ተው!… የእድሜ ነገር አይነሳ፡፡ አንተም ተቆፍረህ ስላልወጣህ እንጂ ወንዱ ሉሲ ነህ፡፡ በርግጥ እኔም ዳይኖሠር ጋልቤአለሁ፡፡
ቁልሉ፡- እስቲ ከዚህ በፊት ስለሰራኸውና ከዚህ በኋላ ስለምትሰራው ስራ ንገረን
ፍልፍሉ፡- እንደምታውቀው እኔ በቪሲዲ ደረጃ የመጀመሪያ ሥራዬ ከማስተር ፊልም ፕሮዳክሽን ጋ የሠራሁት ትዝታና ጨዋታ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አንዳንድ ሥራዎችን ሠርቻለሁ፤ እስከአሁን ግን አልወጡም፡፡ ምናባት በቀጣይ ጊዜያት ሊወጡ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን ደስተኛ አያደርጉኝም፡፡
ቁልሉ፡- ለምን?
ፍልፍሉ፡- ደስተኛ እሆን የነበረው እዚያ የዐዕምሮ ደረጃ ላይ እያለሁ ቢወጡ ነበር፡፡ ገና ያልበሰለና ያልዳበረ አዕምሮ እያለኝ የሠራኋቸው ናቸው፡፡ አሁን በብዙ መልኩ ተቀይሬአለሁ፡፡ ትልቅ የዐዕምሮ ብስለትና የሙያ እውቀት አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህ የያኔዎቹን ስራዎች አሁን ያለው አዕምሮዬ ብዙም ሊቀበለው አይችልም፡፡
ቁልሉ፡- ሥራዎቹ ከዚህ በኋላ ቢወጡም ህዝቡ የድሮ ስራዎችህ እንደሆኑ ስለሚለይ አንተን በእነዚያ ስራዎች እንደማይመዝንህ አምናለሁ፡፡
ፍልፍሉ፡- አዎ! እኔም ስራዎቹ አሁን ባለው የአዕምሮ ደረጃዬ የተሰሩ እንዳልሆኑ እንዲታወቅልኝ ነው የምፈልገው፡፡
ቁልል፡- ስለቀጣዩ ጊዜስ ምን እያሰብክ ነው?
ፍልፍሉ፡- እንግዲህ ከዚህ በኋላ እኔና አንተ በጥምረት ብዙ ስራዎችን በ‹‹ፍልቅልቅ›› እንደምንቀጥል ነው የሚሠማኝ፡፡ ‹‹ፍልቅልቅ›› አንድ ወጥቷል፡፡ በቅርቡም ፍልቅልቅ ሁለት ይወጣል፡፡ ከዚያም ፍልቅልቅ ሶስት፣አራት … እያለ ይቀጥላል፡፡ ቁጥርና እኛ እስክናልቅ ፍልቅልቅ አይቆምም፡፡
ቁልሉ፡- ህይወት እንዴት ናት?
ፍልፍሉ፡- እግዚአብሔር ይመስገን ጠይም ናት፡፡ አትከፋም አትለማም ተመስገን ነው፡፡… እስቲ ምን አይነት ባህሪ እንዳለኝ ንገረኝ፡፡ የዋህነቴና ደግነቴ ምን ያህል እንደሆነ ለአንባቢያን እንዲሆን አድርገህ ተናገረው
ቁልሉ፡- አብዛኛው ሠው በቲቪ የሚያይ ስራችንን እንጂ እውነተኛ ማንነታችንን አያውቅምና ጥያቄህ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ እንግዲህ አንተ ከሰው የመግባባት ልጅ ተሰጥኦ አለህ፡፡ ግልፅ ነህ፡፡ ነገር ግን ቸልተኝነት አለብህ፡፡ በጣም የምጠላው ባህሪህን ደግሞ ሰው ቀጥረህ ሞባይልህን የምታጠፋት ነገር ነች፡፡ አንዳንዴ ሲ.አይ.ኤ እየፈለገህ ያለ ሁሉ ይመስለኛል፡፡
ፍልፍሉ፡- ሞባይሌን የማጠፋው ራሴን ከማጠፋ ብዬ ነው፡፡… ዋናው ምክንያቱ ይሉኝታና ሠው አለማስቀየም ነው፡፡ ከሠዎች ጋር የቁም ነገር ቀጠሮ ኖሮኝ ስገናኝ ስልኬ አርባ ሠባት ጊዜ ከየአቅጣጫው ይደወልበታል፡፡ ከነዚህ ደዋዮች ውስጥ ብዙዎች መጥተው ሊወስዱኝ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ስለዚህ የቁም ነገር ቀጠሮዬን ለማሣካት ወይም አብሮኝ ያለውን ሠው ላለማስቀየም ስል ስልኬን እጠፋለሁ፡፡
ቁልሉ፡- መቼስ ሞባይል የሚያገልግለው መረጃ ለመቀያየር ነው፡፡ የት ነህ? እንዴት ነህ? ልንባባልበት ዘመኑ ያበረከትልን ልዩ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ አንተ እንዳልከው ይህ ላለማስቀየም እዚያኛው ላይ ከመዝጋት ይልቅ ሲደውል ከሰው ጋር እንደሆንክና እንደማይመችህ መንገር ነው የሚሻለው፡፡
ፍልፍሉ፡- አልለምድ ያልኩት ነገር ነው እንግዲህ ወደፊት አሻሽላለሁ፡፡
ቁልሉ፡- ጎሽ! ሲመክሩት እሺ ብሎ የሚሠማ ልጅ ደስ ይላል፡፡ በኋላ ስንወጣ ከረሜላ እገዛልሃለው እሺ
ፍልፍሉ፡-እሺ ደስታ ከረሜላ ነው የምፈልገው፡፡
ቁልሉ፡- በል ደግሞ ስለ እኔ ባህሪ ንገረኝ
ፍልፍሉ፡-ያው ታስነቅለኛለህ፡፡ አንድ ቀጠሮ ላይ አስር ደቂቃ ካረፈድኩ ለአስር ሠዓት እንዳብድ አድርገህ ታሽረኛህ፡፡ ከዚህ ውጪ ከሰው ጋር ያለህን አቀራረብና ከእኔ የበለጠ ቁም ነገረኛነትህን እወድልሃለው፡፡ አንዳንድ መ/ቤቶች አብረን ስንሄድ ከእኔ ይልቅ አንተ ነህ በትዕግስት ጉዳዩን አስረድተህ የምታሳምነው፡፡ ተነጋግረም ሣንግባባ ስንቀር እኔ ቶሎ እበሳጫለሁ፡፡ አንተ ግን በትዕግስት ለማስረዳት ትሞክራለህ፡፡ ይሄ በጣም የምወድልህ ባህሪህ ነው፡፡
ቁልሉ፡- እስቲ ስለ ስፖርት እናውራ… ኳስ ትወዳለህ?
ፍልፍሉ፡- ኦ! ፉትቦል… እኔ በበኩሌ ኳስና ዳንስ አይሆኑኝም፡፡
ቁልሉ፡- ለምን?

ፍልፍሉ፡- በህይወቴ ኳስን አንድም ቀን መትቻት አላውቅም፡፡ እሷ ነች መጥታ የምትመታኝ፡፡ ተመልካች ሆኜም ከህዝቡ ለይታ የምትመታው እኔን ነው፤ ምን እንዳደረኳት አላውቅም፡፡
ቁልሉ፡- በረኛ ሆነህ ስለሆንከው እስቲ ንገረኝ … የሚያወቁህ ሠዎች እንኳን ኳስ የአደራ ገንዘብ መያዝ እንደማትችል ሲናገሩ ሠምቻለሁ፡፡
ፍልፍሉ፡- አዎ!… አሞና የሚባል የሠፈራችን ቡድን አሠልጣኝ በረኛ አድርጎኝ እየተጫወትን ሳለ አንድ የተናቀናቃኝ ቡድን ተጫዋች ኳሷን አክርሮ ሲመታት እንቅ አድርጌ ቀለብኳት፡፡ እሷን እቅፍ አድርጌ እንደያዝኩ ቆሜ ወደ ሜዳው ሣይ የዕኛ ልጆች ተክዘው ቆመዋል፡፡ የተቀናቃኙ ቡድኑ ተጫዋቾች ደግሞ ይጨፍራሉ፡፡ ምን ሆነው ነው የተከዙት? ብዬ ማሰላሰል ውስጥ ገባሁ፡፡ ኳሷን እንቅ እንዳደረኩ ወደ ህዝቡ ስመለከት ከፊሉ ተክዟል ከፊሉ ይጨፍራል፡፡ በኋላ ነገሩ ግራ አጋብቶኝ ቆሜ ሳለ አሠልጣኛችን በጎሉ ጀርባ ነጥቶ ‹‹ሆድህ ቀዳዳ ነው›› አለኝ፡፡ ዞር ብዬ ሣይ ኳሷ መረቡ ውስጥ ነች፡፡ የያዝኩት ሆዴን ነው፡፡ የእውነት ሆዴ ተቀዶ ኳሷ የሾለከች መስሎኝ ሆዴን ፈትሼዋለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሠፈር ልጆች በረኛ ስደርሳቸው ያለቅሳሉ፡፡
ቁልሉ፡- እኔ የማልረሳው ድሮ ጃንሜዳ ኳስ ስንጫወት በፕሮጀክት ታቅፈን በምንጫወት ሰዓት ዜሮ ሶስት ቀበሌ የሚባል ቀበሌ አለ ወደ ጃንሜዳ፡፡ ኳስ በጣም ጎበዞች ናቸው፡፡ ከእነርሱ ጋ ለዋንጫ ጨዋታ በደረስን ጊዜ የእኛ ደጋፊ ዘጠኝ ናቸው፤ የእነርሱ ጃሜዳ ሙሉ ነው፡፡ ሁሉም ችቦ ይዟል፡፡
ፍልፍሉ፡- እናንተን ሊያበሯችሁ ነው?
ቁልሉ፡- ታዲያ… እኛም ጠንካሮች ነን እነሱም አይበገሩ ፡፡ በኋላ ጨዋታው መሀል ከላይ ከጎሉ ጀርባ መጥተው ‹‹ በቃ ለኮስንህ›› ይሉኛል፡፡ ጥቂት ይቆዩና ‹‹ቂጥህ ነደደ›› ይሉኛል፡፡ በየደቂቃው እየሽማቀቅኩ ቂጤን ቼክ ሳደርግ ቆይቼ እግዜር ይስጠው ተካላካያችን የራሳችን ጎል ላይ ኳሷን ሲነክራት ጃንሜዳ እንዴት ትልቅና ተሩጦ የማያልቅ እንደሆነ ያወቅኩት ያኔ ነው፡፡
ፍልፍሉ፡- እስቲ እኔም አንድ ልጨምር… የእኛ ጎረቤት አቶ ተስፋዬ ዘውዴ የሚባሉ አሉ፡፡ የህግ ጠበቃ ናቸው፡፡ የእሳቸው ልጆች ሁልጊዜ ከፍለፍሉ ጋር ነው የምንበላው ይላሉ፡፡ ከእሱ ጋር ካልሆነ አንበላም ስለሚሉ እኔ ጋር እንዲበሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ምግብ በልቶ የጨረሰ አንድ ለስላሳ ስለሚሽለም ዘለው እኔ ጋር ይመጡና ለእኔ ነው የሚሰጡኝ እኔ ደግሞ ጥርሴ እስኪግል ነው የምበላው፡፡
ቁልሉ፡- አውቃለሁ!… ከአፍህ እንፋሎት ሲወጣ ነው የምታቆመው፡፡
ፍልፍሉ፡- አዎ! መጥገቤን ባልንጀራዬ ነው የሚነግረኝ፡፡ ያንን ጥርግ አድርጌ ስበላላቸው‹‹ማሚ ጨረስን›› እያሉ ወደ ለስላሳው ይሮጣሉ፡፡ የሚገርመኝ ግን እስከአሁንም ያ ቤተሰብ ጉዴን አያውቀውም፡፡ ያወቀ እለት ወዮልኝ፡፡ በኋላ ላይ ትንሹ ልጅ ታሞ ሳጫውተው ቆየሁ፡፡ የዚያን ዕለት ፕሮግራም ስለነበረኝ ሱፍ ስለብስ ከውጪ የመጣ ሬሣ ነው የምመስለው፡፡ ግን ግዴታ ስለሆነብኝ ለብሻለሁ፡፡ በኋላ ከረባቴን እየጎተተ ሣሎኑን በዳዴ ያዞረኛል፡፡
ቁልሉ፡- ውሻው ነው?
ፍልፍሉ፡- አታዳምጥም ማለት ነው፡፡ የታመመው ልጅ አልኩህ… እያጫወትኩት ሲጎትተኝ እንድትቆጣው ብዬ እናትየውን ቀና ብዬ ሳያት ‹‹ጎበዝ ቤቢን አጫውተው›› አለችኝ፡፡ ይህ አልበቃ ብሏት ‹‹ቤቢዬ ተጫወት እንደውም ጀርባው ላይ ውጣ›› አለችው፡፡
ቁልሉ፡- በጣም ያዘንክበት ቀን መቼ ነው
ፍልፍሉ፡- ኧረ! እኔ መቼ ደስ ብሎኝ ያውቃል?
ቁልሉ፡- አሁን አሁን እንኳን ደህና ነህ፡፡
ፍልፍሉ፡- እንግዲህ እኔ በጣም አዘንኩበት የምለው ቀን ከቤት የወጣሁበትን ነው፡፡ ራሴን ችዬ ለመኖር ከቤተሰቦቼ ቤት ወጥቼ በችዬን መኖር ከጀመርኩበት ቀን በቁም የተቀበርኩበት ያክል ያዘንኩበት ነው፡፡ ራሴን ቻልኩ ብዬ ራሴን ላጠፋ የነበረበት ቀን መቼም አይረሳኝም፡፡ አንተስ?
ቁልሉ፡- እኔ ደግሞ የኪነ ጥበብ ህይወት ውስጥ የገባሁበት ቀን ነው፡፡
ፍልፍሉ፡- ምነው?
ቁልሉ፡- እንዴት ምነው ትላለህ …? እስቲ ከእኛ ህይወት ውስጥ ማነው በሙያው ደስታን የተጎናፀፋት፡፡ እኛ እንሠራለን፡፡ እውቅናው አለ ተጠቃሚው ግን ሌላ ነው በዚያ ላይ ልተውህ ስትለው አይለቅም፡፡ እንደ አሚር ከያዘ ያዘ ነው፡፡ ለማንኛውም እስቲ ስለጓደኞችህ እናንሳና የሆነ ነገር ትዝ አለኝ፡፡
የምታስተወዋውቀኝ የድሮ ጓደኞችህ ወይ እንዳንተ የፊት ጥርስ የላቸውም፡፡ ወይ ግንባራቸው ተበይዷል፡፡ ወይ አፍንጫው ተተርትሯል መንታዎችህ ነው የሚመስሉት… ምክንያቱ ምንድን ነው?
ፍልፍሉ፡-አስገባህልኝ! ወይኔ!… ሁላችንም እንደፈጣን ተፋፍቀን አለቅን፡፡
ቁልሉ፡- አንተ ብዙ ሰዎችን ታስቃለህ አንተን የሚያስቅህ ማነው?
ፍልፍሉ፡-እኔንጃ!… ብዙ ኮሜዲያን አሉ፡፡ እከሌን ብሎ ለይቶ መናገር ይከብደኛል፡፡
ቁልሉ፡- በሀገራችን ኮሜዲና ኮሜዲያን አለ?
ፍልፍሉ፡- በትክክል አለ
ቁልሉ፡- ቁጥራችን በቂ ነው?
ፍልፍሉ፡- እንዴት ተደርጎ!… ለሰባ ምናምን ሚሊዮን ህዝብ በጣት የሚቆጠሩ ኮሜዲያን እንዴት በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ የሀገራችን ህዝብ ራሱ በጣም ኮሜዲ ነው፡፡
ቁልሉ፡- ኑሮው እኮ ነው ኮሜዲ ያደረገው፡፡ ኑሮ ከአቅም በላይ ሲሆንበት ህይወት በቀልድ መግፋት ጀምሯል፡፡ ታክሲ ውስጥና ካፌዎች አካባቢ የምሰማቸው ቀልዶች እኛ ኮሜዲያኑ ከምናቀርባቸው የላቁ ናቸው፡፡ በተለይ ወጣቱ ሁሉም ቀልደኛ ሆኗል፡፡
ፍልፍሉ፡- ህዝቡ የሚቀልደውን ያህል እንዳንቀልድ እኮ ገደቡም ተፅእኖ አለው፡፡ እኛ እንዳንቀልድ ገደብ የተጣሉብን ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ በመሠረቱ የአንድ ኮሜዲ ተልዕኮ ሣቅ መፍጠር እስከሆነ ድረስ ገደብ ሊበጅለት አይገባም ነበር፡፡
ቁልሉ፡- ልክ ነህ!… የኮሜዲ ተልዕኮ በማኛውም ነገር ላይ መቀለድና መሣቅ እስከ አሁን ድረስ ገደብ ሊደረግ አይገባውም ነበር፡፡ የእኛ የኮሜዲያን አላማችን ህበረተሰብን ማሣቅ ነው፡፡ በማንኛውም ርእሰ ጉዳይ ላይ ሣቅ የሚፈጥር ነገር መናገር ስለማንችል ህዝቡ በቀልድ በልጦን ሄዷል፡፡ በየቤቱና በየሠፈሩ የሚሳቅባቸው ጉዳዮች በእኛ አፍ እንዳይነገሩ ገደብ መጣሉ አግባብ አይመስለኝም ፡፡ ፈጠራን ያቀጭጫል፡፡
ፍልፍሉ፡-ህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ጉዳዮች እየተነሱ ሣቅ እንዲፈጠርባቸው ካልተቻለ የኮሜዲ ሙያ በዚህች አገር የት ቦታ እንደሚደርስ እድሜ ከሠጠን አብረን እናየዋለን፡፡ በመሠረቱ እንዳንቀልድባቸው የተከለከሉት ሁሉ አዲስ ነገሮች አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ እኛ አሳምረን እናቀርባቸው እንደሆነ እንጂ ሁሉም የሚታወቁና ውስጥ ውስጡን እየተሳቀባቸው ያሉ ናቸው፡፡
ቁልሉ፡- መፍትሔው ምን ይመስልሃል?
ፍልፍሉ፡- እኔ መድሃአለም ይፍታው ነው የምለው፡፡
ቁልሉ፡- አመሰግናለሁ፡፡ S


Post your comment

Comments

  • alemayehu bazezew Added yehe ene yeserahut interview new source balemetekesu aznalehu
Watch new Ethiopian movies. Visit the new Sodere.com website or download the mobile application for iPhone and Android. Choose your phone type. iPhone   Android     iPad

Related Articles

RSS